የጽ/ቤቱ ስራ አጀማመር፣ ዕድገትና ህጋዊ መሠረት

በየትኛውም የዓለም ሀገሮች እንዳለው ሁሉ በአገራችንም ሰነዶች የማረጋገጥ፣ የመመዝገብ እና የማስቀመጥ ሥራ የተጀመረው በሀገሪቱ ዘመናዊ ሕጎች ከመቀረፃቸውና ተግባር ላይ ከመዋላቸው በፊት ሲሆን ይኼውም በተለያዬ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ እንደነበር የተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ በግለሰቦች ተይዞ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ስራውን የሚያከናውን ተቋም የውል ክፍል፣ የውል ዋና ክፍልና የመሳሰሉት ስያሜዎች እየተሰጠው በከፍተኛ ፍርድ ቤትና በአውራጃ ፍርድ ቤት፣ በፍትህ ሚኒስቴር ወይም በህግና ፍትህ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ስራውን ሲያከናውን እንደቆዬ፣

የኢህዲሪ የመንግሥት አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 8/1980 የፍትህ ሚኒስቴር የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤቶችን የማደራጀትና በበላይነት የመቆጣጠር ሥልጣን እንደተሰጠውና በዚሁ ስር ተደራጅቶ እንደነበር፣

በ1985 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 41/1985 መሰረት ጽ/ቤቱ ከፍትህ ሚ/ር ወጥቶ በቀድሞ የክልል 14 መስተዳደር የፍትህ ቢሮና የክልል ፍርድ ቤት ስር ተዋቅሮ መደራጀቱ፣

ከ1988 ሚያዝያ ወር ጀምሮ ራሱን ችሎ በጽ/ቤት ደረጃ ተዋቅሮ የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት በመባል ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አድርጎ አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆየቱ፣ (በዚሁ ወቅትም የማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 26/1993 በምክር ቤቱ እንደወጣለት)፣

በ1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ ቀደም ሲል በህግ ተቋቁሞ ሲሠራ የነበረው “የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት” በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በክፍል ደረጃ ለመስተዳድሩ ጽ/ቤት ተጠሪ ከነበረው የልደትና ጋብቻ ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመቀላቀል ”የውልና የክብር መዝገብ ማስረጃ አገልግሎት” በሚል ስያሜ እንዲደራጅ በከተማው የአስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 2/1995 መሠረት ተወስኖ ራሱን የቻለ ህጋዊ ተቋም ሆኖ በምክር ቤቱ በጀት ተመድቦለትና በካቢኔው ኃላፊ ተሹመለት እስከ ሰኔ 1998 ዓ.ም በዚሁ መልክ ሲሠራ የቆየ መሆኑ፣

የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ በመላ አገሪቱ ተፈፃሚነት የሚኖረው አንድ ወጥ የፌዴራል ህግ ቢመራ በዜጐች መካከል የሚከናወኑ የንግድና ሌሎችንም የኢኮኖሚ እና ህጋዊ ግንኙነቶች በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በመታመኑ ይህንኑ ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት በህግ በመደንገግ አዋጅ ቁጥር 334/1995 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመውጣቱ የአሁኑ ተቋም በአዋጁ መሰረት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ተብሎ እንዲሰየም መደረጉ፣

ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ በ1995 ዓ.ም አጋማሽ አካባቢ ፀድቆ በነጋሪት ጋዜጣ ቢወጣም ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ሳይገባ እስከ 1997 ዓ.ም ከቆዬ በኋላ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 467/1997 መውጣት ምክንያት አዋጁ ወደ ተግባር መለወጥ እንቅስቃሴ በመጀመር ተጠሪነታቸው ለየከተማው መስተዳድር ምክር ቤቶች ተደርገው እንዲቋቋሙ በአዋጁ ታስበው የነበሩ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤቶች ተጠሪነታቸው ለፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር ሆኖ በአዋጁ የተዘረዘሩትን ተግባራት እንዲያከናውኑ መደረጉ፣

ለአሠራር እንዲያመች ተጠሪነቱ በቀጥታ ለፍትህ ሚኒስቴር እንዲሆን በአዋጁ ላይ የተቀመጠለት የድሬዳዋ ጽ/ቤትም ተጠሪነቱ አዲስ አበባ ለሚገኘው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት እንዲሆን በደብዳቤ መመሪያ በመሰጠቱ እንደ አንድ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሆኖ በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑ፣

Posted in Uncategorized.